የውሃና የእሳት ጥምቀት የጌታንም ቃል አስታወስኩ፥ እርሱም። ዮሐንስ በውሃ አጥምቆአል፤ እናንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ፤ የሐዋርያት ሥራ 11:16
ወንጌሎች ማቴዎስ 3:1-17 1 በዚያም ወራት መጥምቁ ዮሐንስ። 2 መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ አለ። 3 በነቢዩ በኢሳይያስ። የጌታን መንገድ አዘጋጁ፥ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ ሰው ድምፅ የተባለለት ይህ ነውና። 4፤ ዮሐንስም የግመል ጠጉር ልብስ ነበረው፥ በወገቡም የቆዳ መታጠቂያ ነበረ፤ ሥጋውም አንበጣና የዱር ማር ነበረ። 5፤ ያን ጊዜ ኢየሩሳሌምና ይሁዳ ሁሉ በዮርዳኖስም ዙሪያ ያለች አገር ሁሉ ወደ እርሱ ወጡ፤ 6፤ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ከእርሱ ተጠመቁ። 7. ነገር ግን ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ብዙዎች ወደ ጥምቀቱ ሲመጡ ባየ ጊዜ፥ እንዲህ አላቸው። እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቁጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ? 8 እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤ 9 በልባችሁም። አብርሃም አባት አለን እንደምትሉ አታስቡ፤ እግዚአብሔር ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆችን ሊያስነሣለት እንደሚችል እላችኋለሁና። 10፤ አሁን ደግሞ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጧል፤ ስለዚህ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። 11 እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ ጫማውንም ልሸከም የማይገባኝ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤ 12 መንሹም በእጁ ነው፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥ ስንዴውንም ወደ ጎተራው ይከታል፥ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል። 13፤ በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ። 14 ዮሐንስ ግን። እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን? ብሎ ከለከለው። 15 ኢየሱስም መልሶ። አሁንስ እንዲሁ ፍቀድልኝ፤ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው። ከዚያም ፈቀደለት። 16 ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውሃ ወጣ፤ እነሆም፥ ሰማያት ተከፈቱለት፥ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ፤ 17 እነሆም፥ ድምፅ ከሰማይ መጥቶ። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ።